
በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት መካከል በጋራ በሚሰሩ ጉዳዮች ዙሪያ ዉይይት ተደረገ።
በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት መካከል በጋራ በሚሰሩ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም በአዋጅ ቁጥር 1178/2012 መሰረት በሰዉ መንገድ፤ ሰዉን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ሰውን በህገወጥ መልኩ ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀሎች ተከላካይ የትብብር ጥምረት ከፌዴራል ፍትህ ሚኒስቴር ጀምሮ በከተማ አስተዳደሮችና በክልሎች በፍትህ ተቋማት ሥር ተቋቁሞ መደበኛ ባልሆነው ፍልሰት ምክንያት የሚደረሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታትና የዜጎችን ህይወት የመታደግ ጉዳይ መንግስት ትልቅ ትኩረት የሰጠበት ጉዳይ በመሆኑ በትብብርና በተቀናጀ ሁኔታ መስራት እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ተነስቷል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ በተለይም የከተማ አስተዳደሩ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በአዋጁ 1178/2012 መሰረት በከተማው ካቢኔ ደንብ ቁጥር 126/2014 ከማፅደቅ ጀምሮ በቢሮ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት በማቋቋም በወንጀሉ ዙሪያ ግንዛቤን በመፍጠር ፣ ወንጀል መከላከልና ህግ ማስከበር ፣ የወንጀሉ ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን መብት ጥበቃና መልሶ የሚቋቋሙበት ሁኔታ በማመቻቸት እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበርና ነፃ የስልክ ጥሪ 6073 አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ ጀምሮ የተሻለ ሥራ እየተሰራ የሚገኝ ቢሆንም ከችግሩ ውስብስብነትና ተለዋዋጭነት አንፃር ተጨማሪ ሥራ ከብሔራዊ ፍልሰት ትብብር ጥምረት ጋር በተቀናጀ ሁኔታ መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።
በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው ትብብር የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ጉዳዮች በተለይም ነፃ የስልክ ጥሪ ተደራሽነት ጉዳይ፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ፣ ተጎጂዎች መብት ጥበቃ ዙሪያ፣ የወንዶች ምስክርና ተጎጂ ማቆያ ማዕከል ጉዳይ ፣ ከሌሎች ክልሎች ጋር ያለዉን የግኑኝነት አግባብ ማጠናከርና የህዝብ ንቅናቄን መፍጠር ፣ የአገር ዉስጥ ሰዉ መነገድ ወንጀሎች ዙሪያ እንዲሁም የሥራ ስምሪት ኤጀንሲዎችን መከታተልና መቆጣጠር ጉዳዮችን በተመለከተ በጋራ በመሰራት የበለጠ ዉጤት ማምጣት እንደሚቻል አመላክተዋል ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ብርሃኑ ከብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጋር በመተባበር ለመስራት የተደረገው ዉይይት እጅግ ጠቃሚ እና ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል ።
ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.