
በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ተገለፀ ።
ይህ የተባለው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በሰው መነገድ ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ተከላካይ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከሚሽን ፎር ዴቬሎፕመንት ፕሮግራም (MCDP) ከተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር በሕጻናት መብት ጥበቃ ዙሪያ ስልጠና በተሰጠበት ወቅት ነው።
በስልጠናው የአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊውን ጨምሮ ዓቃቢያነ ህግ እና ከ11ዱም ክፍለ ከተማ የትብብር ጥምረቱ ተጠሪዎች ተገኝተዋል።
በወቅቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትብብር ጥምረት ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ብርሃኑ እንደተናገሩት ከተማችን የዓለም አቀፍ ዲፕሎማት መቀመጫ ፣ የአፍሪካ መዲና ብሎም የሀገራችን ርዕሰ ከተማ በመሆኗ ወደ ከተማዋ የሚደረገው ህገወጥና ኢ-መደበኛ ፍልሰት ምክንያት የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን እያስተናገደች ትገኛለች ።
በተለይም ያሉት ኃላፊው ህገ ወጥ የህፃናት ዝዉዉር ፣የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ፣ ህፃናትን ለልመና ተግባር ማዋል፣ ህፃናትን ለወንጀል ተግባር መጠቀም ፣ የሰውነት አካል ስርቆት ፣ ለወስብ ጥቃትና መሰል የመብት ጥሰቶች ብለዋል ።
የጽ/ቤት ኃላፊው አክለው ህጻናት ሁሉን አቀፍ እንክብካቤ እንዲያገኙ ፣ እንዲማሩ በህግ ልዩ ጥበቃ ከተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚመደቡ ስለሆነ ከተለያዩ ጥቃትና መብት ጥሰት መጠበቅ ከቤተሰብ ጀምሮ በሁሉም አካለት ላይ የተጣለ ግዴታ በመሆኑ ይህ ታሳቢ ተደርጎ የዛሬ ህፃናትን የነገ ሀገር ተረካቢዎችን መብት በሙሉ አቅም ማክበርና ማስከበር ግድ በሚልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ያሉ ሲሆንበህፃናት መብት ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩ ሁሉም ባለድርሻዎች ከወትሮ የተለየ አካሄዶችን በመተግበር በልዩ ሁኔታ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል ።
የሕጻናት መብት ጥበቃ ጋር በተያያዘ በሐገር አቀፍ እና በአለማቀፍ ደረጃ የተደነገጉ ህጎች ዙሪያ በወይዘሮ ሚስጢረ አፈወርቅ ለውይይት መነሻ ሰነድ ቀርቦ ተሳታፊዎችም ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ያላቸዉን አስተያየትና ጥያቄ አቅርበዋል ።
በመጨረሻም ከቤቱ ለተነሱ ሃሳብ እና ጥያቄዎች የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ እና የMCDP ፕሮግራም ተወካይ የሆኑት አቶ ምኞት ወ/የሱስ በጋራ ምላሽ በመስጠት አጠቃለዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.