
ቢሮው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በሰው የመነገድ ወንጀልን መከላከል የሚያስችል ውይይት አካሄደ ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ህይወት ኢትዮጵያ ከተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር ከቢሮና ከሁሉም ክ/ከተማ ዐቃቢያነ ህግ ፣ ከአአ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ፣ ከዕድር ምክር ቤት ተወካዮች ፣ ከፍልሰት ተመላሾች ድርጅቶችና ከሚዲያ ከተወከሉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሰዉ መነገድና ሰዉን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል መከላከልን አስመልክቶ ውይይት ተደርጓል ።በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በፍትህ ቢሮ በሰው መነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ተከላካይ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ብርሃኑ እንዳሉት ዕድሮች በሰው መነገድና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከል በደንብ ቁጥር 126/2014 እንዲሁም የአ/አ/ከተማ የዕድሮች ምክር ቤት ቁጥጥርና ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ ቁ. 151/2016 መሠረት ዕድሮች ለአበላቶቻቸዉ ስለ ወንጀሉ አስከፊነት ግንዛቤ በመፍጠር፣ ጥቆማ በመስጠት፣ ከህግ አካላት ጋር በመተባበር ማህበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አንፃር በተለይም ኢ- መደበኛ ፍልሰትን በመግታት ሂደት ዉስጥ ዕድሮች ያላቸው ሚናን በመረዳት በሕጉ የተሰጣቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ እና በዕድሮች መተዳደሪያ ደንብ ዉስጥ የፍልሰት ጉዳይን በማካተትና አጀንዳ በማድረግ አባላቱንና ቤተሰቡ ከወንጀሉ እንዲጠብቁ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል።ኃላፊው አክለው ወንጀሉ እጅግ አስከፊ የተደራጀ እና ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ምላሾችም የተደራጁና በትብብር መሆን አለበት በማለት የህዝብ ተሳትፎ በወንጀል መከላከል ሂደት ዉስጥ ጎልቶ እንዲወጣ የማድረግ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል ።የህይወት ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው ድርጅቱ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የተገበራቸውን ዋና ዋና ተግባራት በማቅረብ ዕድሮች ወንጀሉን በማስመልከት በመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ በማድረግ ከሚመለከታቸው አካል ጋር በቅንጅት በመስራት እና ጥቆማዎችን እንዲሰጡ በማድረግ በዕድሮች መተዳደሪያ ደንብ/መመሪያ ለአፈጻጸሙ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እድሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ታምራት ገ/ማርያም ስለ እድሮች ምንነትና ተግባራት እንዲሁም ዕድሮች ህጋዊ በመሆን ከቀብር ማስፈፀም ባሻገር በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች በተለይም በሰው መነገድ ወንጀልን ጨምሮ በሌሎችም የሰላምና ልማት ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት ጋር በመተባበር እየሰሩ መቆየታቸውን ገለጻ አድርገዋል።በመጨረሻም በእድሮች መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ወንጀል ጉዳዮችን አስመልክቶ እንዲካተቱ በጋራ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ የፊርማ ስነስረዓትም ተካሂዷል ።በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለተነሱት ግብአት እና ጥያቄዎች የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ብርሃኑ እና የአ.አ ከተማ እድሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ታምራት ገ/ማርያም ምላሽ በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል ።
መስከረም 20/2018
ፍትሕ ቢሮ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.