በበይነ መረብ አማካይነት የሚፈፀም ህገወጥ የሰዎ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በበይነ መረብ አማካይነት የሚፈፀም ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል መከላከልና ህግ ማስከበር ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሂዷል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከንጋት ግሎባል ኢንሼቲቭ ጋር በጋራ በመተባበር በበይነ መረብ አማካይነት የሚፈፀም በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ለመከላከል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው።በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፍትህ ቢሮ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ ወርቁ  እንዳሉት በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ዜጎችን ለከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ እየዳረገ መሆኑን በዚህም የተማሩና ግንዛቤ ያላቸው ወጣቶች በበይነ መረብ አማካይነት  በውሸት ተስፋ ተታለው በተለይም ወደ ደቡብ ምስራቅ ኤዥያና ሌሎች አገራት በመሄድ ለሰው መንገድ ወንጀል ሰለባ በመሆናቸው በዚሁ ዙሪያ የሚሰሩ  የግንዛቤ ስራዎችና የሕግ ማዕቀፍ ተፈጻሚነት ይበልጥ ማጠናከር  እንደሚገባ ገልጸዋል።የንጋት ግሎባል ኢንሼቲቭ ፕሮግራም ከፍተኛ ኦፊሰር የሆኑት ዶ/ር ፉፋ ኢሳያስ በንጋት ግሎባል ኢንሼቲቭ አጠቃላይ በሰው መነገድ ወንጀል ከመከላከል ጀምሮ ተጎጂዎችን እስከ ማቋቋም ድረስ  የተሰሩ ስራዎች እንዲሁም የተመዘገቡ አፈጻጸሞችና ስኬቶችን በሰነድ አቅርበዋል።በፍትሕ ቢሮ በሰው የመነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ተከላካይ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ብርሃኑ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ዘመኑ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ መስፋፋትና ሰው ሰራሽ አስተውሎ (AI) በመጠቀም ከሚፈፀሙ ከባባድ ወንጀሎች አንዱ በመሆኑ በተለይም ወጣቱ የተሳሳተ ውሳኔ ከመወሰን በፊት በቂ መረጃ እንዲያገኝ በዚሁ ጉዳይ ላይ ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑና ወንጀሉን ከመከላከል ጀምሮ የሕግ ማዕቀፎችን በአግባቡ መተግበር፣ ሕገ-ወጥ ደላሎችንና አዘዋዋሪዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንዲሁም የተጎጂዎችን መብትና ደህንነት ማስጠበቅና የትብብር ማዕቀፍ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን በንግግራቸው ተመላክቷል።

 

በዕለቱ በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ዙሪያ የአለም አቀፍ፣ አህጉራዊና የሀገራችን የህግ ማዕቀፍ እንዲሁም የአሰራር  ሥርዓቶችን በተመለከተ ወንጀሉን ለመከላከል በወጡ አዋጆች በተለይም በአዋጅ ቁጥር 1178/2012 ላይ የውይይት ሰነዱን ያቀረቡት በፍትህ ቢሮ የትብብር ጽ/ቤት ዐቃቤ ህግ ወ/ሮ ሚስጥር አፈወርቅ ናቸው  ።

 

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ሃሳብ አስተያየት በተሰጡት ጉዳዮች ዙርያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ አማካሪ አቶ አዝመራ በዳዳ፣ የፍትህ ቢሮ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ ወርቁ እንዲሁም የንጋት ግሎባል ኢንሼቲቭ ፕሮግራም ኦፊሰር ዶ/ር ፉፋ ኢሳያስ  አወያይነት እና  ምላሽ በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል።

ፍትሕ ቢሮ

ህዳር 15/2019 ዓ/ም


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.