
በመዲናዋ ከስድስት ሺህ በላይ የግል አቤቱታ መዛግብት በዕርቅ ተቋጭተዋል
በመዲናዋ ከስድስት ሺህ በላይ የግል አቤቱታ መዛግብት በዕርቅ ተቋጭተዋል- ቢሮው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ባለፉት ሰባት ወራት በግል አቤቱታ የቀረቡ ከ6 ሺህ በላይ የወንጀል መዝገቦች በዕርቅ እንዲቋጩ መደረጉን የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ገለጸ፡፡
የፍርድ ቤት ማስማማት አገልግሎት የመፍትሔ ሃሳቦችን የሚያቀርብ የማቀራረብና የማስማማት ስራ በሚሰራ ባለሙያ አጋርነትና አደራዳሪነት የሚደረግ በነፃ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ፤ በፍርድ ቤት በተቋቋሙ የማስታረቅ አገልግሎት ቢሮዎች ውስጥ የሚደረግ የስምምነት ሂደት ነው፡፡
የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ተክሌ በዛብህ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ወደ 8 ሺህ 999 የሚጠጉ የወንጀል መዛግብት የመመርመርና ማጥራት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
ከዚህም ውስጥ ምርመራቸው የተጠናቀቁ 7 ሺህ 197 የግል አቤቱታ መዛግብት መሆናቸውን አንስተው 6 ሺህ 292 መዛግብቶችን ጉዳያቸው በዕርቅ መዝጋት መቻሉን ተናግረዋል።
በግል አቤቱታዎችና በደንብ ጥሰት ክርክር ላይ ከነበሩ ከ3 ሺህ 08 የወንጀል መዛግብት ውስጥ 2 ሺህ 115ቱ በፍርድ ቤት ውሳኔ ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል።
ቢሮው በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ አካባቢዎች የንቃተ ህግ ግንዛቤ በማሳደግ በስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋ የመፍጠር ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በቢሮው ባሉት ስድስት ነፃ የስልክ መስመሮች ለሚመጡ ጉዳዮች የሕግ ምክሮችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው በተለይም በሰው መንገድና በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ላይ ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.