
ጥምረቱ በአፈፃፀም ሪፖርቱና በማስፈፀሚያ ዕቅዱ ላይ ተወያየ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በሰው መነገድና በህገወጥ መንገድ ማሻገር ወንጀሎች ተከላካይ የትብብር ጥምረት በ2017 የ9ወራት አፈፃፀም ሪፖርትና በ3ኛው የፍልሰት ምክር ቤት ማስፈፀሚያ እቅድ ላይ ተወያየ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ ዣንጥራር አባይ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት የጥምረት ፅ/ቤቱ በፍትህ ቢሮ ስር ሆኖ ቴክኒካል ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።
በተለይም ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ላይ ጥሩ በሚባል ደረጃ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የመጀመሪያው ስራ ግንዛቤ መፍጠር ነው ያሉት ም/ከንቲባው የውጪ ሀገር የስራ ስምሪት በህጋዊ መንገድ እንዲከወን ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።
ስለሆነም የየክፍለ ከተማው የስራና ክህሎት ቢሮዎች ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ከመከላከል ባሻገር ለስራዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የፍትሕ ቢሮ ኃላፊው አቶ ተክሌ በዛብህ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ በሰው መነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ለመከላከል ተቋማዊ ተደርጎ ስራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስተው በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሰሩትን ብቻ ለአብነት ብንወስድ ከብዙ በጥቂቱ ፣
በመድረክ እና የተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በመጠቀም በሰው መነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል መከላከል ላይ ለ822,492 ህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ለመፍጠር ታቅዶ በመድረክ ለ69,291 ፣ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለ1,802,249 ህብረተሰብ ክፍሎች፣ በአጠቃለይ 1,871,540 ህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ መፈጠሩንና ሌሎች ተከታታይ ስልጠናዎች፣ ድጋፋዊ ክትትሎች፣ አደረጃጀት ለማጠናከር የተሰሩት የሚጠቀሱ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ፍትህ ቢሮ ህግ የማስተባበር ኃላፊነት ከተሰጡ ስራ ቡድኖች ሕግ የማስከበርና ወንጀል መከላከል ስራ ቡድን ስር በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በ9 ወራት ውስጥ 100 የወንጀል መዝገቦች ተጣርቶ 55 መዝገቦች ስልጣን ላለው አካል ተልኮ ክስ የተመሰረተ ሲሆን ቀሪ 45 መዝገቦች በምርመራ ሂደት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በ6073 የነፃ የጥሪ ማዕከል ከማህበረሰቡ በአጠቃለይ የቀረቡ 157 የጥቆማ ጥሪዎች ሲሆን ከዚህ ውስጥ 6ቱ ከወንጀል ጋር በተያያዘ መረጃ፣ 30 የሕግ አስተያያት፣116 አግባቢነት የሌለው ሲሆኑ 5 በሰው መነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል የሚያሟሉ በመሆናቸው ምርመራ እንዲመራበት ተደርጓል፡፡
ሆኖም ከችግሩ ውስብስብነት አንጻር አሁንም ምላሹ በቂ ባለመሆኑ የሁሉም አካላት ልዩ ርብርብ ይፈልጋልም ብለዋል ኃላፊው፡፡
በውይይቱ የየክፍለከተማው ስራ አመራሮች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አጋር አካላት ተሳታፊ ነበሩ።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.