ደንብ ቁጥር 206/2018 የመንግሥት ሠራተኞች የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ተቋም ሥልጣንና ተግባር፣አደረጃጀት
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ብቃትን መሠረት ያደረገ የሰው ሀብት ሥራ አመራር እና ልማት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋትና ተግባር ላይ ማዋል በማስፈለጉ፤ የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች በዕውቀት፣ በክህሎት እና መልካም ባህሪያት እንዲታነጹ እና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል የብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፤ የመንግሥት ሠራተኛ የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ሥራዎችን በግልጽነት፣ በቅንጅት፣ ወጥ በሆነ መንገድ በመተግበር እና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናን በማሻሻል የዜጎችን እርካታ እና በተቋማት ላይ ያላቸውን አመኔታ ለማሳደግ ሲባል የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ተቋም ሥልጣንና ተግባር፣ አደረጃጀት እና አሰራሩን በሕግ መወሰን አስፈላጊነቱ በመታመኑ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በከተማው አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር ፹፯/፪ሺ፲፯ አንቀጽ ፲፯ ንዑስ አንቀጽ (፪) በተደነገገው መሰረት ይህን ደንብ አውጥቷል፡፡