ደንብ ቁጥር ፩፻፶፪/፪ሺ፲፭ የአዲስ አበባ ንግድ ሥራዎች ድርጅት ለማቋቋም የወጣ ደንብ
በአዲስ አበባ ከተማ የንግድ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲሁም የነዋሪው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ እና ሌሎች በአለም አቀፍና በሀገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ የተለያዩ ምክንያቶች የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ ለኑሮ ውድነት አንዱ ምክንያት በመሆኑ፤እና በተፈጠረው የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር እና በመካከለኛ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል የግብርናና የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን እና የንግድ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በቀጥታ ከአርሶ አደሩ፣ ከማምረቻና ከአከፋፋይ በመግዛት ለከተማው ነዋሪና አስተዳደር የሚያቀርብ የመንግስት የልማት ድርጅት ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር ፫፻፷፩/፲፱፺፭ አንቀፅ ፲፩ ንዑስ አንቀጽ (፪) ተራ ፊደል (መ) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሠን በወጣው አዋጅ ቁጥር ፸፬/፪ሺ፲፬ አንቀጽ ፺ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህን ደንብ አውጥቷል፡፡