ደንብ ቁጥር ፻/፪ሺ፲፮ የአዲስ አበባ ከተማ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ማቋቋሚያ ደንብ
የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ እና የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የሚከበርበት፣ ድሉን የሚዘክሩ ቅርሶች እና ታሪኮች የሚጠበቁበትና የሚጎበኙበት፣ በታሪኩ የሚኮራ ተመራማሪ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል ሙዚየም ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ የአንድነት ምልክት፣ የጀግኖች አርበኞች መዘከሪያ፣ ለአዲሱ ትውልድ ማስተማሪያ ፣ የአድዋ ድል ታሪክን ለትውልድ ለማስተላለፍና ጠብቆ ለማቆየት እንዲሁም ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ጎብኝዎች የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ በማስፈለጉ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለነፃነታችንና ለአንድነታችን የተከፈለውን መስዋዕትነት ከመዘከር ባሻገር የአሁኑ ትውልድ እያከናወናቸው ያሉ ለመጪው ትውልድ የሚሸጋገሩ ሥራዎችን የሚያስተሳስርበት፣ ትውልድን ለመቅረጽና ለማስተማር የሚያለግል እና ሌላ የጀግንነት ታሪክ የሚገለጥበት የሕጻናት ሙዚየም ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑን በማመን፤