ህትመቶች

180/017 የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ

image description

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፵፬ ንዑስ አንቀጽ (፩) እና አንቀጽ ፺፪ ንዑስ አንቀጽ (፩) ሁሉም ሰዎች ንጹሕና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንደአላቸውና መንግሥትም ንጹሕና ጤናማ አካባቢ እንዲኖራቸው የመጣር ኃላፊነት እንደአለበት የተደነገገ በመሆኑ፤ በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር ፫፷፩/፩ሺ፱፺፭ አንቀጽ ፱ ንዑስ አንቀጽ (፰) የከተማው አስተዳደር የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ከተማውን የተፈጥሮ ሚዛኑን የጠበቀ፣ ጽዱ፣ አረንጓዴና ምቹ ማድረግ በዓላማ ደረጃ የተደነገገለት በመሆኑ በከተማው ውስጥ የሚገኙ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸው ንጹሕና ጤናማ አካባቢ እንዲሆኑ ማድረግ በማስፈለጉ፤ በከተማው ውስጥ የሚገኙ ወንዞችና የወንዝ ዳርቻ እና ገባሮቻቸው ከተለያዩ የመኖሪያ ቤቶች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም ፋብሪካዎች በሚወጣው በካይ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች ምክንያት ተፈጥሯዊ ባህሪ ተቀይሮ ለሰዎች ጤናና ደህንነት ጎጂ በመሆናቸው፤ የከተማዋን ወንዝና ዳርቻውን ከብክለት በመጠበቅና በማስተዳደር፤ እንዲሁም የተፈጥሮ ይዘቱን እንዳይቀይር በማድረግ፤ የሰውን ጤንነት፤ ከማስጠበቅና ህይወት ያላቸውና የሌላቸውን በወንዝና በወንዝ አካባቢ የሚኖሩትን የተፈጥሮ ሥነ-ህይወታዊ አካላትን ማቆየትና ማስቀጠል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ የወንዝ ብክለትን ለመከላከል የተቀመጡ አሰራሮች ተግባራት በማይፈጽሙ አካላት ላይ ተመጣጣኝ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ከጥታፋቸው ተምረው ከተመሳሳይ ድርጊት እንዲታቀቡና የደረሰውን ጉዳት በማስተካከል ወደነበረበት እንዲመልሱ ማድረግ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት በሕግ መዘርጋት አስፈላጊነቱ ስለታመነበት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር ፹፬/፪ሺ፲፮ አንቀጽ ፺፬ መሰረት ይህንን ደንብ አውጥቷል፡፡