184/2017 መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ሥርዓት ለማስያዝ የወጣ ደንብ

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱ በመደበኛው የንግድ ሥርዓት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑን በመገንዘብ ይህንን ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድ በሥርዓት ካልተመራ በከተማ ውበትና ገጽታ፤ በከተማ ጽዳት፤ በትራፊክ ፍሰትና እንቅስቃሴ፤ በኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት እና በከተማዋ ሰላምና ፀጥታ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትል በመሆኑ፤ መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድ የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማግኘትና የሚያስከትላቸውን ችግሮች መቅረፍ የሚቻለው ዘርፉ ህጋዊ ሆኖ በሥርዓት ሲመራ በመሆኑና ዘርፉን ሥርዓት በማስያዝ በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ወደ መደበኛ የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ቀደም ሲል በሥራ ላይ የነበረው መደበኛ ያልሆነ የንግድ ሥራ ለመምራትና ሥርዓት ለማስያዝ የወጣው ደንብ ቁጥር ፹፰/፪ሺ፱ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም በማድረግ መተካት በማስፈለጉ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር ፹፬/፪ሺ፲፮ አንቀፅ ፺፬ መሠረት ይህንን ደንብ አውጥቷል፡፡