አዋጅ ቁጥር ፲/፲፱፻፺፯ ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጤና አገልግሎት አሰጣጥ አስተዳደርና አመራር አዋጅ
በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የጤና ተቋሞች አንድ ወጥ በሆነ የአሠራር፣ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት እንዲመራ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃውን የጠበቀ እና በሥርዓት የሚመራ እንዲሆን ማድረግ በማስፈለጉ፤ በመከላከል ላይ የተመሠረተውን የጤና አገልግሎት በሥልጠናና በሕክምና አገልግሎት እንዲደገፍ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፤ በከተማ ውስጥ የጤና ተቋሞች ስለነባርና አዲስ ስለሚከሰቱ በሽታዎች እና የእነዚህም ሥርጭት ስላስከተለው ውጤት ከተማ አቀፍ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ በመታመኑ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋሞችን አደረጀጀትና የሥራ አመራር ማሻሻል፣ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ የጤና ተቋሞች ጋር ያላቸው ግንኙነት የሠመረ እንዲሆን ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስትዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር ፫፻፲፩/፲፱፻፺፭ አንቀጽ ፲፬ (፩) (ረ) እና ፷፮ (፪) መሠረት የከተማው ጊዜያዊ አስተዳደር ይህንን አዋጅ አውጥቷል፡፡